
የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሴናተሮቹ ክሪስ ኩንስ እና ክሪስቫን ሀሎን ከሰሞኑ ወደ ሱዳን ያቀናሉ ተባለ፡፡ ሴናተሮቹ በመጪው ሰኞ ወደ ካርቱም ያቀናሉ የተባለ ሲሆን ከሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጀነራል አብዱልፋታህ አል ቡርሀን እና ከጠቅላይ ሚኒሰትር አብደላ ሀምዶክ ጋር እንደሚወያዩ የሱዳን የዜና አገልግሎት /SUNA/ ዘግቧል፡፡
ሱና ሴናተሮቹ የሱዳን-አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚጎለብትበትና የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ውዝግብ በሚፈታበት ዙርያ ከተለያዩ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ብሏል፡፡ ገዳሪፍ አካባቢ የሚገኘውን ኡም ራኩባ የኢትዮጵያውያን ስደተኞች መጠለያ ጣቢያን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተነገረው፡፡
መጠለያ ጣቢያው በትግራይ ግጭት ምክንያት የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ተጠልለው የሚገኙበት ነው፡፡ ሴናተር ክሪስ ኩንስ ከአሁን ቀደም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በትግራይ እና በሌሎችም ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር መነጋገራቸው ይታወሳል። ምንጭ አል ዓይን ኒውስ፣ ሱና