
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ከታዩት የህትመት ሚዲያዎች መካከል ከፍ ያለ ተነባቢነት እና ዝናን አትርፋ የነበረችው የ“አዲስ ነገር” ጋዜጣ ባልደረቦች ከነበሩት መካከል አንዱ የሆነው ታምራት ነገራ ዳግም ለስደት ተዳርጓል።
ታምራት ነገራ እና የአዲስ ነገር ባልደረቦች በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ይመራ ከነበረው መንግሥት በገጠማቸው ጫናና ስጋት ከአገር ተሰደው ለዓመታት መቆየታቸው ይታወሳል። ነገር ግን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ ባካሄዱት ለውጦች ተበረታተው ወደ አገር ቤት ከተመለሱት የጋዜጣዋ ባልደረቦች መካከል ታምራት ነገራ አንዱ ነው።
ለዓመታት ከቆየባት አሜሪካ የተመለሰው ታምራት ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን በመስጠት እና በመንግሥት ላይ ጠንካራ ትችቶችን በመሰንዘር ይታወቃል።
ኋላ ላይም “ተራራ ኔትወርክ” የተባለውን የራሱን የዩቲዩብ ቻናል በመጀመር ዜና እና ትንታኔዎችን ሲያርብ ቆይቷል። ነገር ግን ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ መጀመሪያ ላይ በፀጥታ ኃይሎች ከቤቱ ተወስዶ ለአራት ወራት ያህል በእስር ከቆየ በኋላ በዋስ መፈታቱ ይታወሳል።
ታምራት መጋቢት ወር ማብቂያ ላይ ከእስር ከተፈታ በኋላ ወደ ሥራው ሳይመለስ ለወራት ድምጹ ሳይሰማ ቆይቶ ባለፈው ሳምንት ከባለቤቱ ጋር ዳግም ወደ ስደት ተመልሷል። ታምራት አሁን እንዳይጠቀስ ከፈለገው በስደት ካለበት ስፍራ ስለእስሩ፣ በዝምታ ስለቆየበት ምክንያት፣ ስለወደፊት ዕቅዱና ስለሌሎች ጉዳዮች በተለይ ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል።
ቢቢሲ፡ መሰደድህን የሚገልጥ ዜና ባሳለፍነው ሳምንት ተመልክተናል። በርግጥም ስደትን መርጠሃል? ለምን?
ታምራት ነገራ፡ አዎ መሰደዴን የሚገልጸው ዜና እውነት ነው። ለመሰደድ የወሰንኩባቸው ምክንያቶች ግልጽ ናቸው። የታሰርኩበት ሁኔታ፣ ከታሰርኩ በኋላ ብሎም በዋስ ከተለቀቅሁ በኋላ ወደ ጋዜጠኝነት ለመመለስ የሚያስፈልጉ ነገሮች አልተሟሉም። እንዲያውም አደጋዎች እየጨመሩ መጡ።
የኦሮሚያ ፖሊስ ስታስር የወሰዳቸው ከ32 በላይ የስቱዲዮ እቃዎችን አልመለሰልኝም። ይሄ የእኔ ብቻ ሳይሆን የተራራ ኔትወርክ ሠራተኞች ንብረት የሆኑም ይገኙበታል።
ባለቤቴ ሰላም በላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤት፣ ፖሊስ ኮሚሽን በመሄድ “ታምራት ላይ ክስ ትመሰርታላችሁ ወይ፣ ምርመራ ጨርሰናል ብላችኋል፣ ንብረታችንን ትመልሳላችሁ ወይ?” የሚሉ ጥያቄዎችን በማመልከቻ ጭምር አቅርባ ነበር። ያገኘችው ምላሽ ግን “አይበቃችሁም ወይ?”፣ ወደ ሥራም ለመመለስ ታስባላችሁ ወይ?” በሚል ማስፈራሪያው ከእኔ አልፎ ቤተሰቤ ላይ እና ሠራተኞች ላይ መምጣቱ ሌላው የመሰደዴ ምክንያት ነው።
ማስፈራሪያው እየጨመረ መጥቶ ለቅሶ ቤት፣ ሠርግ ወይም በአደባባይ ከተገኘሁ “ለምን ዐይንህን እናያለን?” የሚሉ የደኅንነት እና የፖሊስ ኃይሎች እየታዩ ስለመጡ አገር ውስጥ መኖር አሳሳቢ እየሆነ መጣ።
ከእኔ ባሻገር ግን ሌሎች ጋዜጠኞች ላይ የሚደረገው እስር እና እንግልት ብሎም በአጠቃላይ ሚዲያ ላይ የሚደረገው አፈና እየበረታ መምጣቱ በቀጣይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ የሚዲያ ሥራ መስራት ይቻላል የሚለውን እምነቴን ሙሉ ሉሙሉ ስለዘጋው፣ የሚዲያ ሥራውንም ለመስራት ብሎም በሰላም ለመኖር ከአገር መውጣት አስገዳጅ ሆኖ ስላገኘነው እኔ እና ባለቤቴ ወጥተናል።
ባለፉት ወራት ታስሬ በነበረበት ብሎም ከተፈታሁ በኋላ ከፍርድ ቤት፣ ከዐቃቤ ሕግ፣ ከፖሊስ ብሎም ተራራ ኔትወርክን ማስተዳደርን ጨምሮ ይህንን የሕይወት ጉዞ ያለ ባለቤቴ ሰላም በላይ እገዛ እና አብሮነት ላልፈው አልችልም ነበር።
ብዙዎች ከሚያውቁት በላይ ነው የሰላም ሚና። ተራራ እንዲቋቋም ብሎም በእግሩ እንዲቆም ያደረገችው። አንደኛው እንድሰደድ ምክንያት የሆነኝም ባለቤቴን ወደ እነዚያ 7 ቀናት ውስጥ መልሶ ለመውሰድ የሚያስችል ጭካኔ ስለሌኝ ነው።
ከብዙ የቤተሰብ እና የግል የኑሮ ጫና ጋር በፖሊስ፣ በፌደራል ብሎም በክልል ዐቃቤ ሕግ፣ በፍርድ ቤት ምን አይነት እንግልት እንደደረሰባት ለመናገር አልችልም። ስለዚህ አንዱ ለመሰደድ እንድመርጥ ያደረገኝ በእሷ ትከሻ ላይ የነበረው ጫና ነው። አብረን እንድንሰደድ ያደረገው አንዱ ምክንያትም እሱ ነው። ቢቢሲ፡ በቁጥጥርስር ከዋልክ በኋላ ያለህበትን ለማወቅ እና ፍርድ ቤት እስከምትቀርብ ድረስ 7 ቀናት ጠይቋል። የት ነበር የተወሰድከው? እነዚያ የነበረህ ቆይታ ምን ይመል ነበር?
ታምራት ነገራ፡ በቁጥጥር ስር ከዋልኩ በኋላ ለ7 ቀናት ፍርድ ቤት አልቀረብኩም፣ ቤተሰብም የት እንዳለሁ ማወቅ አልቻለም ነበር። በወቅቱ ወደ ገላን ከተማ ተወስጄ በኦሮሚያ ልዩ ኃይል ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ነበር የቆየሁት። ካምፕ መሆኑን ያወቅሁት በቁጥጥር ስር ያዋሉኝ ፖሊሶች ዩኒፎርማቸውን በማየት ነው።
ይህ ካምፕ የኢትዮጵያ መንግሥት ብሎም የኦሮሚያ ልዩ ኃይል የግድያ እና የስቅይት ካምፕ ነው። ለሰባት ቀናትም ለብቻዬ ከሌሎች ታሳሪዎች ጋር በማልገናኝበት ክፍል ውስጥ ነበር የታሰርኩት። በእነዚህ ቀናት ለእኔ የጮሁ ሰዎችን በሙሉ በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ስም ማመስገን እፈልጋለሁ። ይህ ጫና ባይኖር ኖሮ ምን አልባትም በሕይወት ላልኖር እችል ነበር።
ቢቢሲ፡ ከተፈታህ በኋላ ዝምታን መርጠህ ነበር። ለምን? ከዚያስለምን ተመልሰህ ወደ ሚዲያህ አልመጣህም?
ታምራት ነገራ፡ ዝምታን የመርጥኩበት ብዙ ምክንያቶች አሉ። አንደኛው እንደተፈታሁ ለመናገር ያሰብኳቸው ብዙ ነገሮች ነበሩ። በተለይም እስር ቤት ውስጥ ያገኘኋቸው በፖለቲካም፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ሆነ የፖለቲካ አቅጣጫ ላይ የማልስማማቸው ብዙ ሰዎችን አግኝቻለሁ።
ነገር ግን እነዚህ ሰዎች አጽንተው የተናገሩት እዚህ እስር ቤት ያየኽውን ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነህ እንድትናገር አንፈቅድልህም ነው ያሉኝ። ከቤተሰቤም በፊት ማለት ነው።
በተለይም ጃል አብዲ ረጋሳ [የኦነግ ከፍተኛ አመራር እና በእስር ላይ ያሉ ፖለቲከኛ] በዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በግሉም ሆነ በቤተሰቡ ላይ ብዙ መከራ፣ ስቃይ ብሎም ከፍተኛ የሚባለውን ግፍ ካዩ ሰዎች አንዱ ይመስለኛል። እርሱ አጥብቆ ያስጠነቀቀኝ ነገር፣ “ከኢትዮጵያ ሳትወጣ የምንነግርህንም ሆነ ያየህውን ነገር እንዳትናገር” ብሎ ነው።
ሁለተኛው የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ በተቀበሩ የጨለማ እስር ቤቶች ውስጥ የሚፈጽመውንና ያየሁትን ሳልናገር ወደ ሚዲያ ሥራው መመለስ አልችልም። እንደ ጋዜጠኛም ሆነ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ይህንን ሳልናገር ሚዲያ መስራት አልችልም። ይህንን የይምናገርበት ቀን ይመጣል። ብዙ መረጃዎች የያዘዝኩት አለ። ይህንንም በቅርቡ ይፋ አደርጋለሁ።
ያንን እንዳላደርግ የእነ ጃል አብዲ ማስጠንቀቂያ ብሎም ቤተሰብ አለ። ሦስተኛው ደግሞ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው እውነታ ለሚዲያ የሚመች አይደለም። ስለዚህ የምናገር ከሆነ፣ የምናገረው እውነት መሆን አለበት።
እውነትን ለመናገር ደግሞ እውነትን ለመናገር የሚቻልበት ቦታ ላይ መሆን ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት እውነትን ለመናገር የሚቻልበት ቦታ ናት ብዬ አላምንም። ሁኔታዎች ከተቀየሩ ብዬ 7 ወር ያህል ቆየሁኝ። ያለው ነገር ይበልጥ እየባሰ መጣ።
ቢቢሲ፡ በስደት ከምትኖርበት አሜሪካ ስትመለስ ይዘህ የመጣህውን ተስፋ እና አሁን ለዳግም ስደት ስትዳረግ ያለህን ስሜት አነጻጽረህ ንገረኝ እስቲ?
ታምራት ነገራ፡ የዛሬ አራት መት ከስደት ተመልሼ ስመጣ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙዎቻችን ተስፋ ነበረን። አሁን ተስፋ አስቆራጭ ነገር አለ። ተስፋ የቆረጥኩት አሁን ባለው መንግሥት እና አገዛዝ እንጂ በኢትዮጵያ አይደለም። ሥርዓቱ ተስፋ የሚቆረጥበት ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ላይ ተስፋ አልቆርጥም።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚዲያ ሥራ ለመስራት አስቸጋሪ ነው። ሚዲያ አንዱ ጎኑ ንግድ ነው። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት የትኛውንም ንግድ ለማንቀሳቀስ ያለው ሕገ መንግሥት፣ ብሔርተኝነት እና ዘረኝነት እየታየ ሥራ ለመስራት የሚቻልበት ሆኖ አይታይም።
ስለዚህ ከአራት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲታይ አሁን ያለው ነገር ተስፋ ያስቆርጣል፤ ተስፋ የምንቆርጠው ግን በገዢዎቹ ላይ እንጂ በኢትዮጵያ ላይ አይደለም።
ቢቢሲ፡ ከዚህ በኋላ ወደ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ትመለሳለህ?
ታምራት ነገራ፡ የመገናኛ ብዙኃን ሥራ በውስጤ ስለሆነ የትም ብሄድ፣ ምንም ቋንቋ ብናገር ከውስጤ የማይቀር ሥራ ስለሆነ አይቀርም። ስለዚህ ወደ መገናኛ ብዙኃን ሥራ እመለሳለሁ። እመለሳለሁ ብቻ ሳይሆን የተራራ ኔትወርክ የኢትዮጵያዊነት ድምጽ መሆኑን ይቀጥላል።
ተጠናክረን እና ከባለፈውም በበለጠ ነጻ በሆነ ሁኔታ ይቀጥላል። ስለኢትዮጵያ ተስፋ መስጠታችንን፣ ማስተማራችን እና ድምጽ መሆናችን አይቀርም።
ቢቢሲ፡ በቆይታህ ካከናወንከው ውስጥ ማድረግ አልነበረብኝም እና ሳላደርግ የቀረሁት የምትለው?
ታምራት ነገራ፡ ከመታሰሬ አንድ ቀን በፊት ሦስት አዲስ ተመራቂ ልጆችን ቀጥረን ጨርሰን ነበር። ሙሉ ሂደቱን ጨርሰን ነበር። እና በጣም የሚቆጨኝ ወጣቶችን እና የሚቀጥለውን ትውልድ አገሬ ውስጥ ሆኜ ያለችኝን መጠነኛም ብትሆን የጋዜጠኝነት እውቀት ላሳያቸው እፈልግ ነበር።
የዲጂታል ጋዜጠኝነትን በአዲስ መልኩ መስራት ፈልጌ ነበር። የተራራ ኔትወርክን ለመደገፍ በተሰበሰበ ገንዘብ የተገዙ የስቱዲዮ እቃዎች በመንግሥት እጅ ውስጥ ወድቀዋል። ነገር ግን እሱ አይደለም የሚያሳስበኝ። የሚያሳስበኝ ለወጣት ጋዜጠኞች በአገሬ ውስጥ ሆኜ ጋዜጠኝነትን ለማሳየት ባለመቻሌ ነው።
ቢቢሲ፡ ወደ ኢትዮጵያ መቼ እመለሳለሁ ብለህ ታስባለህ? ኢትዮጵያ እንዴት ሆና እንድትጠብቅህ ትፈልጋለህ?
ታምራት ነገራ፡ ወደ ኢትዮጵያ ልመለስ እችላለሁ፤ ሁኔታዎች ከተቀየሩ። ዋናው የሚያሳስበኝ ግን መመለስ ያለመመለስ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ ውጪ ላለው የምትሆን አገር እንዴት ነው ማድረግ የሚቻለው የሚለው ጥያቄ ነው የሚያሳስበኝ። ይሄ ደግሞ የእኔ ብቻ ጥያቄ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነው።
በዚህ ላይ ያለኝን አስተዋጽኦን ከውጪም ሆኜ ቢሆን አበረክታለሁ ብዬ አምናለሁ። ኢትዮጵያውያን የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ እስከምናይ ድረስ አናቆምም። አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ለማንም የምትሆን አይደለችም።
ሁልጊዜ እንደምለው እስራኤላዊያን እስራኤል ከፈረሰች ከሁለት ሺህ አመት በኋላ መልሰው ገንብተዋታል። ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ እንዳለባት ሁላችንም እናውቃለን።
ኢትዮጵያ እንድትቆም የምንፈልገው ሰዎች ብንችል በዘመናችን እናቆማታለን፤ ባንችል በቃል አቁመናት ያ ቃል ነገ ከሺህ ዓመታትም በኋላ ይሁን ኢትዮጵያን መልሶ የሚሰራ እንዲሆን ማድረግ ግዴታ አለብን ባይ ነኝ።
ቢቢሲ፡ በቅርቡ ከኢሠፓ መልሶ ምሥረታ ጋር ስምህ በተደጋጋሚ ተነስቶ ነበር። በዚህ ዙሪያ ምን ምላሽ አለህ?
ታምራት ነገራ፡ ከኢሠፓ ምሥረታ ጋር ስሜ መነሳቱ ለእኔም ዜና ነው። ምንም የማውቀው ነገር የለም። እኔ የኢሠፓ አባልም ደጋፊም አይደለሁም። በወቅቱ ግን ይህንን ማስተባበል አስፈላጊ ስላልነበረ አላስተባበልኩም። ከዚህ በተጨማሪ ግን ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ግንኙነት እንዲኖረኝ አልፈልግም።
በወጣትነት ዘመኔ ከቅንጅት ጋር ተሳትፌያለሁ፤ ተመራጭ ነበርኩ። ፖለቲካ ፓርቲን ከምሥረታው በቅርብ ርቀት አይቼዋለሁ። ቅንጅትን ያፈረሱትም ሆነ ለማሰቀጠል የሞከሩት አመራሮች ጋረ በቅርበት ሰርቼ የፖለቲካ ፓርቲን አሰራር ኢትዮጵያ ውስጥ ምን እንደሆነ አይቼዋለሁ። እኔ የፖለቲካ ፓርቲ ኢትዮጵያን ያድናል የሚል እምነትም የለኝም። ለዚህም ነው ወደ ሚዲያ ሥራ የማተኩረው።