
ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ተሳታፊዎች 11 የተለያዩ ሞባይል ስልኮችን የሰረቀ ግለሰብ በቁጥጥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።ተጠርጣሪው የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው ህዳር 11 ቀን 2015 ዓ.ም በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ሜክሲኮ አካባቢ ነው።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በተካሄደበት በዚህ ዕለት ለተሳታፊዎች ውሃ መርጫ በተዘጋጀበት ስፍራ ላይ የነበረውን የእርስ በርስ መገፋፋት እንደምቹ አጋጣሚ የተጠቀመው ተጠርጣሪው ቦርሳቸውን በስለት በመቅደድ 11 የተለያዩ የእጅ ስልኮችን ሰርቆ ለማምለጥ ሲሞክር በአካባቢው በተመደቡ የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት ነው።
ወንጀሉ ከተፈመባቸው መካከል 8 ግለሰቦች በልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጎማ ቁጠባ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ንብረታቸውን በመለየት ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡ ሲሆን የቀሪዎቹ ሶስት ስልኮች ባለቤቶችም ወደ ጣቢያው በአካል በመቅረብ ንብረታቸውን እንዲለዩ መልዕክት ተላልፏል።