
የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልል ወሰን መካለሉን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተካለሉ አካባቢዎች ላይ የቤት ግብይት እና እግድ አገልግሎት መቋረጡን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካል የነበሩና በአዲስ አበባ ስር የመንግሥት አገልግሎት ሲሰጥባቸው የነበሩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፤ የቤት ሽያጭ፣ ግዢ፣ ሥም ዝውውርና እግድ አገልግሎት ከተቋረጠ በኋላ በአካባቢዎቹ የቤት ግብይት ቆሟል።
ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተካለሉ አካባቢዎች ፋይል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ኦሮሚያ ክልል ርክክብ ማድረጋቸውም ተሰምቷል።
ምንም እንኳን የፋይል ርክክቡ የተከናወነ ቢሆንም፣ የኦሮሚያ ክልል አገልግሎት መስጠት አልጀመረም። ክልሉ ከአዲስ አበባ ከተማ ለተረከባቸው አካባቢዎች መቼ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር እና አገልግሎቱ የት እንደሚሰጥ በውል የታወቀ ነገር አለመኖሩን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተገልጋዮች ተናገረዋል።
ወደ ኦሮሚያ ክልል በተካለሉ አካባቢዎች የቤት ግዢና ሽያጭ እንዲሁም እግድ አገልግሎት ፈልገው ወደ ክፍለ ከተማው የሚያቀኑ ተገልጋዮች፣ አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው እየተቸገሩ መሆኑን ገልጸዋል። አገልግሎቱን ፈልገው አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከተገኙ ተገልጋዩች መካከል ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የባንክ ሠራተኛ፣ ለግል ሥራ ከግለሰብ የተበደሩትን ገንዘብ ለመክፈል ቤታቸውን በዋስትና አስይዘው ከሚሠሩበት ባንክ ብር ለመበደር ቢፈልጉም አገልግሎት በመቋረጡ መቸገራቸውን ጠቁመዋል።
አገልግሎቱን ማግኘት ያልቻሉት ቤቱን እንደ ዋስተና አስይዞ ለመበደር በቅድሚያ የቤት እግድ ለባንኩ ማቅረብ ስላለባቸውና የእግድ አገልግሎት በመቋረጡ ነው። አገልግሎት ፈላጊዎች ቀድሞ አገልግሎቱን ሲያገኙ ወደነበረበት ክፍለ ከተማ ሲያቀኑ የሚሰጣቸው ምላሽ ‹‹ወደ ኦሮሚያ ተካሏል፤ ሄዳችሁ ጠይቁ›› የሚል መሆኑን የባንክ ሠራተኛው ገልጸዋል።
የባንክ ሠራተኛው አክለውም ቦታው ወደ ኦሮሚያ ክልል ቢካለልም የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪነታችሁ ይቀጥላል ከተባለ በኋላ፣ አገልግሎቱ ከአዲስ አበባ መውጣቱ በተገልጋዮች ላይ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ አካል የነበሩና ወደ ኦሮሚያ ክልል የተካለሉ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሆነው እንደሚቀጥሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ ነዋሪዎቹ አገልግሎት የሚያገኙት በኦሮሚያ ክልል እንደሆና ከተማ አስተዳደሩ የፋይል ማዛወር ሥራ ማከናወኑን መስማታቸው ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል።
የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ክልል ወሰን ጉዳይ አወዛጋቢ የነበረ ጉዳይ ሲሆን፣ የወሰን ማካለል ውሳኔ ከተላለፈም በኋላ በተለይ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ነቀፌታ ገጥሞታል። ከፓርቲዎች በተጨማሪ ወደ ኦሮሚያ ክልል መካለላቸውን በድንገት መስማታቸውን የሚገልጹ ወደ ኦሮሚያ የተካለሉ አካባቢ ነዋሪዎች፣ ‹‹ውሳኔ የተወሰነው ሳናውቅና ሳንወያይበት ነው›› በማለት ቅሬታ ማሰማታቸው አይዘነጋም።
መንግሥት በበኩሉ የወሰን ማካለሉ ለአዲስ አበባ ከተማ እና የኦሮሚያ ክልል ወሰን ውዝግብ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ታስቦ የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን እወቁልኝ ማለቱ የሚታወስ ነው። ውሳኔው የፌዴራል መንግሥትን፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልልን እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተርን መሠረት ያደረገ መሆኑንም መንግሥት ገልጿል።
በወሰን ማካለሉ ወደ ኦሮሚያ ክልል ከተካለሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መካከል ኮየ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ በከፊልና ጀሞ ቁጥር ኹለት የሚገኙበት ሲሆን፣ ከኦሮምያ ክልል ደግሞ የኦሮምያ ኮንዶሚኒየም ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲካለሉ ተደርጓል። ይህን የወሰን መካለል ተከትሎ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ክልል የተካለሉ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች ሽያጭ ዋጋ በእጅጉ መቀነሱ ተሰምቷል። ምንጭ አዲስ ማለዳ