
አጃኢባ ያሲን ትባላላች፤ ስልጤ ዞን ተወልዳ፣ ከ4 ዓመት በኋላ ዕድገቷን አዲስ አበባ አደረገች። አስቸጋሪ ሁኔታዎች እና ማኅበረሰባዊ ትችቶች ሳይበግራት ሁሉን አልፋ አሁን ላይ የ12ኛ ክፍል ፈተና በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እየወሰደች ነው።
የአጃኢባን ሕይወት ፈታኝ ከሚያደርጉት ሁኔታዎች መካከል ሁሉንም ተግባራት በሁለት እግሮቿ ማከናወን ሲሆን እሷ ግን ምንም አካል እንዳልጎደለው ሰው ነገሮችን በቀላሉ ታከናውናለች።
“ዋናው ነገር አስተሳሰብ እና አዕምሮ ጠንካራ መሆኑ ነው” የምትለው አጃኢባ፣ የሁለቱም እጆቿ መጻፍ አለመቻል ሳይበግራት በእግሯ እየጻፈች ፈተና በመውሰድ ላይ ትገኛለች።
አጃኢባ ራሷን፣ ቤተሰቧን እና ሀገሯን ለመጥቀም እና ሕልሟን ለማሳካት ዛሬም እየተጋች ነው።
ስትወለድም ያለሁለት እጅ መሆኑን የገለጸችው አጃኢባ፣ ለአቅመ ትምህርት ስትደርስ ነርሰሪ የመማር ዕድል እንዳላገኘች ከኢቢሲ ጋር ባደረገችው ቃለ-ምልልስ ተናግራለች።ሦስት ዓመታትን ኬጂ ለመማር ብትፈልግም ትምህርት ቤቶች ላለመቀበል ሲያንገራግሩ ቆይተው በኋላ 1ኛ ክፍል የመማር አጋጣሚን ስታገኝ ዕድሉን ተጠቅማ ትምህርት መማር እንደጀመረች ተናግራለች።
ከብዙ ወጣ ወረድ በኋላ በእግሮቿ መጻፍ እንደምትችል አባቷ ትምህርት ቤቶችን አሳምነው ትምህርቷን እንድትቀጥል ማድረግ ቻሉ። ከ1ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል የክፍል ባልደረቦቿ በእጃቸው ሲጽፉ አጃኢባ ግን በእግሮቿ እየጻፈች ፈተናዎችን አልፋ ወደ ሌላ ምዕራፍ ለሚያሸጋግራት ለፈተና ደርሳለች።
አጃኢባ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች አልፋ ነው ዘንድሮ ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የበቃችው። ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ የክፍል ባልደረቦቿ በሚጽፉበት ዴስክ ላይ ተቀምጣ በምትጽፍበት ወቅት ለመገመት የሚያስቸግሩ ከባድ ሁኔታዎችን ማሳለፏን ትናገራለች።
የመማሪያ ክፍሏ ውስጥ መቀመጫው ዝቅ ያለ፣ መጻፊያው ዴስክ ደግሞ ከፍ ያለ ስለነበረ አስቸጋሪ ከነበረው ሁኔታ የተሻለ እግሯን ከዴስኩ ጋር ደብተር ለማገናኘት እየተቸገረችም ቢሆን ትጽፋለች።
አሁን ቁጭ ብላ ለመጻፍ እንዲመች ሆኖ መቀመጫ እና መጻፊያ ዴስክ ተሠርቶላት ደብተሯን እና እስክሪፕቶዋን ለማገናኘት ብዙ አልተቸገረችም። አጃኢባ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ስትሸጋገር ትምህርት ቤቱ ከመኖሪያ ሰፈሯ ሩቅ ስለነበረ ከአንዱ ትራንስፖርት ወደ ሌላኛው ስትሄድ ረዳት ያስፈልጋት ስለነበረ ብዙ ትቸግራ እንደነበረ ትናገራለች።
በታክሲ እና በባጃጅ በምትሳፈርበት ወቅት ገንዘብ ካስቀመጠችበት በእግሯ ስትሰጣቸው ብዙዎች ስያንጎጥጧት እንደነበረ ትናገራለች። “ጎበዝም ሰነፍም አይደለሁም” የምትለው አጃኢባ፣ በትምህርቷ አማካይ ውጤት 80 ከመቶ እንደምታስመዘግብ ገልጻ፣ መካከለኛ ተማሪ እንደሆነች ተናግራለች።
ከእህቶቿ ጋር አዲስ አበባ እንደምትኖር የምትናገረው አጃኢባ፣ የኢኮኖሚ ችግር ቢኖርባትም ከምታልመው ለመድረስ እንደማያግዳት ተስፋ በተሞላበት አንደበት ትናግራለች። በዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ያለውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ስርቆትን በመቀነስ ረገድ የሚያስገኘው ፈይዳ ቀላል እንዳልሆነ ገልጻ፣ ተማሪዎች ከቤተሰብ ተለይተው ፈተናውን መውሰዳቸው ጥንከሬን ይሰጣል ብላለች።
ለእሷ ፈተናውን ከቤተሰብ እና ከመኖሪያዋ ርቃ ማከናወኑ ረዳት በምትፈልግበት ወቅት አመቺ ሁኔታ ላይኖር ይችላል፤ ነገር ግን ችግሩን ተቋቁማ ጥሩ ደረጃ ለመድረስ እንደምትሠራ በተስፋ ተናግራለች።
ሰውን የሚጎዳው የአካል ጉዳተኛ መሆኑ ሳይሆን፣ የሥነ-ልቦና ጉዳቱ ነው የምትለው አጃኢባ፣ የብዙዎችን አስተሳሰብ ለመጠገን የሥነ-ልቦና ባለሙያ መሆን የወደፊት ሕልሟ እንደሆነ ተናግራለች። ምንጭ ኢቢሲ