
እስኪ ዛሬ እንደወረደ እንነጋገር! መቸም በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ህዝቦች ዋጋ ከፋይ ናቸው። ዋጋ የማይከፍል የተመቸው ህዝብ የለም። ከጅምሩ የአንድ ቡድን የበላይነትን ለማስፈን በጠማማ መሠረት ላይ የተተከለው መንግስታዊ ስርአት ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝቦች ዋጋ ሲያስከፍል ቆይቷል እያስከፈለም ይገኛል፣ ባልተለወጠ መሠረት ላይ የቀጠለው ስርአታዊ ጉዞም ሀገራችንን ዛሬም ረፍት አልባ አድርጓል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ የአማራ ህዝብ ሰፊ ዋጋ ሲከፍል ቆይቷል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ንጹሀኖች (ህጻናት፣ እናቶችና አዛውንቶች ሳይቀሩ) በብሄር ማንነታቸው ብቻ አማራ ተብለው በጅምላ ይጨፈጨፋሉ፣ ይፈናቀላሉ፣ ይዘረፋሉ። ይህ መከራ የበዛ ብቻ ሳይሆን የተለመደ ሆኗል፤ የሁላችንን የጋራ ውድቀት የሚያውጅ አሳፋሪ ሀገራዊ ሁኔታ ካልሆነ በቀር የአንድ ህዝብ መከራ ብቻ ሆኖ የሚቆም ግን አይደለም።
በተለያዩ አካባቢወች በንጹሀን የአማራ ብሄር ተወላጆች እየደረሠ ያለውን ሞልቶ የፈሠሠ ግፍ በጣም ቀንሰን እንደወረደ ስናስቀምጠው ደግሞ የሀገሪቱ ብልሹ ፖለቲካዊ ስርአት የወለደው የመከራ ጽዋ የመጨረሻ ተቀባይ የወሎ ህዝብ ሆኖ እናገኘዋለን። ሆኖም በዚህ ልክ ፖለቲካዊ ምልከታ ሳያገኝ ዘልቋል !
በተለይ በወለጋ፣ በመተከል፣ በደቡብ ጉራፈርዳና ወዘተ ይሄ ህዝብ ሀገሩ የአዞ ኩሬ ሆናበት ለማያባራ ጅምላ ጭፍጨፋ ስደትና ዘረፋ ተዳርጓል። ከወለጋና ከመተክል በአረመኔወች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ ወሎ የተሠደዱ ንጹሀኖች፣ በጦርነትና ወረራ ምክንያት ለዳግም ስደት ተዳርገዋል።
ይህ ብቻ አይደለም…በክልሉ የሚገኘው የወሎ ህዝብ ለሠፊ ወረራና ውድመት ተዳርጎ ከጉስቁልናው ሳይወጣ የግብር እፎይታ እንኳ የሚሰጠው አካል ባለማግኘቱ ወረራውን ታሳቢ ያላደረገ ግብር እንዲከፍል ተደርጓል፣ ሀገር ግን በዚህ መንገድ አትጠቀምም።
ለአምስት ወራት በወረራ ስር የቆዩት የራያቆቦ፣ የላስታና ዋግ ህምራ አካባቢወች ዛሬም ድረስ ውሀና መብራት አላገኙም። ይህ ብቻ አይደለም….የወሎ አካባቢ በጦርነቱ በተለየ ወድሞ ሳለ ከውድመት እንዲያገግም በሙሉ ልብ ታቅዶ የሚሠራ የማገገሚያና መልሶ ግንባታ ፓኬጅ በተጨባጭ ተጠቃሚ ሲሆን አልታየም። የሠብአዊ ምግብ እርዳታም ቢሆን ለትግራይ ህዝብ ከሚደርሰው የእርዳታ ማእቀፍ እንደ subsidiary የሚገኝ ካልሆነ በቀር (ይህም ካለ) በጦርነት ለተጎዳው ህዝብ ራሱን ችሎ ከጉዳቱ እንዲያገግም በማሠብ የተዘጋጀ የሠብአዊ ድጋፍ ማእቀፍ የለም። የወደመውን መልሶ መገንባትና የተጎዳውን ህዝብ ማቋቋም መቻል የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን ሠብአዊ ጉዳይ ነበር። ይህ ግን የአንድ ሠሞን ወሬ ሆኖ ቀርቷል!
ሁሉም ለሀገሩ ቀናኢ የሆነ ኢትዮጵያዊ እኒህን ጉዳዮች እንዲያጤናቸው ያስፈልጋል። “የባየሽ ማስታወሻ”ን ስናነብ አንድ የወሎ ራያ ሽማግሌ አርሶአደር በጦርነት ወቅት ሞፈርና ቀንበሩን አንስቶ በሬወቹን ጠምዶ ሲያርስ የተመለከቱ …. ምነው ጦርነት መንደራችንን ቀርቦ እያለ አንተ ታርሳለህ? ብለው ይጠይቁታል። ይህም የወሎ አርሶአደር ምንስ ቢሆን መሬት በክረምት እንዴት ጦም ይደር…አላህ ለሰጠው ይሰጣል። እኔ አርሳለሁ አላህ ለኔ ካዘዘውና ከደረስሁበት ፍሬው ለኔ ይተርፋል እኔ እበላለሁ፣ ለኔ ካላዘዘው አላህ ላዘዘው ይተርፋል፣ የሚመጡት ይበሉታል አለ። የዚህ እሴት ባለቤት የሆነ ህዝብ እንዴት ሀገሩ የአዞ ኩሬ ትሁንበት!
ከወሎ እሴት እየሸሸች የምትሄድ ሀገር ሠላም የሚርቃት መሆኑ የማይቀር ነው። ሁላችንም ሀገራችንን ወደ ወሎ እሴት እንመልሳት ዘንድም ጽኑ ምኞቴ ነው! መፍትሄ:- ኢትዮጵያ ሀገራችን የሁሉም ህዝቦቿና የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ክልል እንድትሆን እንስራ!!!