
ኢዜማ በአደረጃጀት ደረጃ የሚመሰገን እና ለሀገር ይጠቅማል ብሎ ያመነበትን አማራጭ ሃሳብን የተሸከመ ፓርቲ ነው ፡፡ በአመራር ስብስብም ቢሆን የተሻለ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ስበስብ ሲሆን በአባላት ተሳትፎ እና ንቃት ደረጃም እንዲሁ ተስፋ የሚጣልበት ድርጅት ነው ፡፡ ባለፉት ሶስት አመታት አመራሩ በተዋረድ ብዙ ሰርቷል ፡፡ ጠንካራም ደካማም ጎኖች ይራሉ ፡፡ የሀገራችን ፖለቲካ ለክርክር ፤ ልውይይት እና ለሃሳብ የበላይነት የሚቀረው መንገድ ገና ብዙ ቢሆንም ይህ ባህል እንዲኖር ብሎም እንዲዳብር ሙከራ እያደረገ ያለ ፓርቲ ለመሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ ፡፡
ኢዜማ ፖለቲካዊ ባህላችን እንዲለወጥ የሚሹ በርካታ አመራር እና አባላት ያሉትን ያክል በነበረው ባህል እንዲቀጥል የሚፈልጉ ፤ ከተለመደው አስተሳሰብ ብዙም ያልተላቀቁም ሊኖሩ ይችላሉ ፡፡ ከነባራዊ ሁኔታዎች ትንታኔ በመነሳት ከገዥው ፓርቲ ጋር የመጣበቅ ወይም የመቀናቀን እሳቤም በፓርቲው ይኖራል ፡፡ ሆኖም ይህ የኢዜማ ችግር ብቻ አይደለም ፡፡ እስከ አሁን ድረስ ከታዩት እና እየታዩ ካሉት ፓርቲዎች ውስጥ የታየ ፤ እየታየም ያለ እውነታ ነው ፡፡ ስልጣን ላይ የነበሩትም ሆነ ያልነበሩት ፓርቲዎች ተሞክሮ የሚነግረን ይህንኑ ነው ፡፡ የመማር እና ያለመማር ፤ የወጣትነት እና የጎልማሳነት አለያም የጾታ ልዩነት ጉዳይ እንዳልሆነ ይታወቃል ፡፡
ኢዜማ በዚህ ሂደት የተሻለ ለመሆን ወይ ሆኖ ለመውጣት መትጋት ይጠበቅበታል ፡፡ ብዙ ጉልበት ፤ ብዙ እውቀት ፤ በጣም ብዙ ግዜ ቢያስከፍለውም የሄደበት መንገድ በበጎም ሆነ በደካማ የተቀመጠ አሻራ እንዳለው ይታመናል ፡፡ ደካማውንም ሆነ ጠንካራ ጎኑን አሁን ቆሞ የሚገመግምበት እና የጎበጠውን የሚያቃናበት ግዜ ላይ ይገኛል ፡፡ ከፊቱ 1ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ይጠብቀዋል ፡፡ ያለፈባቸውን ሶሰት አመታት የሚገመግምበት እና በቀጠይ ሶስት አመታት ሊያሳካቸው የሚፈልጋቸውን አንኳር ግቦች የሚያሰቀምጥበት ፤ እነዚህ ግቦች እንዲሳኩ የተሸለ አመራር ሊሰጡ ይችላሉ የሚላቸውን መሪዎቹን የሚመርጥበት ወቅት ላይ ይገኛል ፡፡ በመሆኑም ግርግር ሳይሆን ስክነት ያስፈልጋል ፡፡ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ፡፡ በቅስቀሳ ወቅት ስርአት እና ጨዋነት በተመላበት ሁኔታ የመሰለውን ሀሳብ የማቅረብ መብት የተመራጩም የአባሉም የደጋፊውም ነው ፡፡ የአንድ ሀገር ዜጎች እንደመሆናችን ለሚቃወመን ወገንም የሚያዳምጥ ጀሮ ሊኖረን ግድ ይለናል ፡፡
ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እና ዲሞክረሲያዊ አሰራሮችን መከተል ሁኔታውን ይበልጥ ለማርገብ እና የፓርቲውን ቀጣይ ግቦች ለማሳካት ወሳኝ ነጥቦች ናቸው ፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚያገለግሉ ተቋማት በፓርቲው ውስጥ ተዘርግተዋል ፡፡ ለተቋማቱ ህግ እና አሰራርም ተዘረግቷል ፡፡ ተቋማቱን እና አሰራራቸውን ማክበር እና ማስከበር በተዋረድ ከአመራሩ እና አባላት ይጠበቃል ፡፡ በዚህ ረገድ አርአያ መሆን ያለበት (በዚህ ግዜ ከጠቅላላ ጉባኤው ቀጥሎ የሚገኘው ) ብሄራዊ ስራ አስፈፃሚው እንደሆነ የብዙዎች አባላት እምነት መሆኑ ይደመጣል ፡፡
በመሆኑም ይህን አካል ጨምሮ በከፍተኛ አመራር ላይ የሚገኙ ወገኖች ከምር ዲሞክራሲያዊያን ኃይሎች መሆናቸውን ማስመስከር ይጠበቅባቸዋል ፡፡ ማስመስከር ይጠበቅብናል ፡፡ ለብዙ ፖለቲካዊ አሰራሮች አርአያ መሆን ፤ ለህዝብ ተስፋ መሆን ይገባል ፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ በዋነኝነት የፓርቲውን ህግ እና ስርአትን በማክበርና በማስከበር ነው ፡፡
በፓርቲ ደረጃ የሚደረገው ምርጫ ከቅስቀሳው ጀምሮ ግልፅ ፤ አሳታፊ ፤ ዲሞክረሲያዊ እና ወንድማማችነት የሰፈነበት ከሆነ እዳው ገብስ ነው ፡፡ የፓርቲው ውስጥ መልካም ልምምድ ለሀገራዊ ምርጫ ሂደት በጎ አስተዋፅኦ ስለሚኖረው ለህዝብ ተስፋ የሚሰጥ ድርጅት እንዲሆን ፓርቲዉን ተመራጭ የሚያደረግ ተግባር ከሁላችን ይጠበቃል፡፡ ለሀገር ዲሞክራሲ ግንባታ መሰረት ለመጣል በኢዜማ ውስጥ ይህን ባህል ለማንበር ስንሰራ ለነበርነው ሁሉ ይህ ጅምር በታላቅ ስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላችንን ሚና ልንወጣ ይገባል ፡፡