
ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ የደረሱበት ሳይታወቅ ከቆዩ ከሁለት ቀናት በኋላ ባሕር ዳር እንዳሉና ደህና መሆናቸውን የሚገልጽ መልዕክት እንደደረሳቸው ባለቤታቸው ለቢቢሲ ተናገሩ። ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞ ሰኞ ግንቦት 08/2014 ዓ.ም. ከቤታቸው ረፋድ ላይ ከወጡ በኋላ የደረሱበት ሳይታወቅ እስከ ረቡዕ አመሻሽ ድረስ ቆይተዋል።
ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን ኃይሌ ረቡዕ ምሽት ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት የጄነራል ተፈራ ጠበቃና የሚያውቋቸው ሰዎች ባለቤታቸው ባሕር ዳር ውስጥ በሚገኘው ዘጠነኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንዳሉ ገልጸዋል። ወ/ሮ መነን ባለቤታቸው በላኩት መልዕክት ደህና መሆናቸውን እና አሁን ያሉበት ቦታ በመግለጽ ቤተሰባቸው እንዲረጋጋ መልዕክት ልከዋል ብለዋል።
ቢቢሲ ይህንኑ በተመለከተ ከአማራ ክልል የፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም ፖሊስ ማብራሪያ ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። የቀድሞው የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ሰኞ ዕለት መሰወራቸውን ተከትሎ ቤተሰቦቻቸው ለደኅንነታቸው ሰግተው የነበረ ሲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስም ሆነ የፌደራል ፖሊስ ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ እንደተነገራቸው ባለቤታቸው ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ባለፈው የካቲት ወር ላይ ከልዩ ኃይል አዛዥነታቸው ተነስተው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አማካሪነት ሹመት ቢሰጣቸው ሳይቀበሉት መቅረታቸው ይታወሳል። ከጓደኛቸው ጋር በነበራቸው ቀጠሮ መሠረት ሰኞ ዕለት ከቤታቸው ወጥተው ሳይመለሱ መቅረታቸውን የሚናገሩት ባለቤታቸው ወ/ሮ መነን የጤንነታቸው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
ጄኔራል ተፈራ ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ያገለገሉ ሲሆን እንዲሁም በቅርቡ የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ሆነው መስራታቸው ይታወሳል ።
ጄኔራል ተፈራ ማሞ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል አዛዥነት ከተነሱ በኋላ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ላይ በመቅረብ የአማራ ክልል እና በፌደራል መንግሥቱ ላይ ትችት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
ወ/ሮ መነን የባለቤታቸውን መጥፋት አስመልክቶ ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ እንዲሁም አዲስ አበባ ፖሊስ በመሄድ ቢጠይቁም ግለሰቡ “በቁጥጥራቸው ስር እንደማይገኙ” ገልጸውላቸው ነበር።
ጄኔራል ተፈራ ማሞ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት ናቸው። ከሚኖሩበት ባሕር ዳር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በእግራቸው ውስጥ የሚገኙትን ጥይቶች በተመለከተ የሕክምና ክትትል ለማድረግ እንደነበረም ጨምረው አስረድተዋል።
የጄኔራል ተፈራ መሰወርን በተመለከተ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምንም መረጃ እንደሌለው ለቢቢሲ ተናግሯል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ሆነው ለዓመታት በከፍተኛ መኮንንነት ያገለገሉት ብርጋዴር ጄነራል ተፈራ ማሞ ከአስር ዓመት በፊት መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሲረዋል በሚል ከሌሎች ጋር ተከሰው ለዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎም ከእስር ተለቀው በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።በቅርቡም የህወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች በመግባት ጥቃት በሰነዘሩበት ጊዜ የክልሉን ልዩ ኃይል በበላይነት ሲመሩ የነበሩ ሲሆን፣ ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ ከዚሁ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጋቸው ይታወሳል። ቢቢሲ