
ሰይፉ ፋንታሁን ከዶ/ር ዳዊት ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ የአእምሮ ህመም አጋጥሞት ህክምና አድርጎ እንደሚያውቅ ተናግሯል። በፊት ይሰራበት ከነበረው ሸገር ኤፍ ኤም ወደ ኢትዮ ኤፍ ኤም ከተዛወረ በኋላ ጭንቀትና ፍርሀት ይሰማው እንደነበረ እንዲሁም በእንቅልፍ ማጣት ይቸገር እንደነበረ ተናግሯል።
በቃለመጠይቁ ላይ የሰይፉ የአእምሮ ሀኪም የነበረው ዶ/ር ዳዊት ህመሙ አዲስ ነገር ውስጥ ስንገባ ለመልመድ ከመቸገር የተነሳ የሚመጣ የአእምሮ መረበሽ (Adjustment disorder) እንደሆነ ተናግሯል። ህመሙ ከታወቀ በኋላ የንግግር የስነልቦና ህክምና አድርጎ እንደተሻለው በቃለመጠይቁ ተገልጿል።
Adjustment disorder ምንድነው?
በህይወት ውስጥ ጫና ሲያጋጥም ጭንቀት ወይም መከፋት የተለመደ ነው። ይሄ ጭንቀት ወይም መከፋት በተለምዶ ከሚጠበቀው ጊዜ በላይ ከቆየ ወይም መጠኑ ከሚጠበቀው በላይ ከሆነ Adjustment disorder(Situational depression) ይባላል።
Adjustment disorder የሚፈጥሩት ጫናዎች አንድ ጊዜ በድንገት የሚከሰቱ አሉታዊ ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ፍቺ፣ የእሳት አደጋ፣ ከስራ መባረር፣ አዲስ ስራ መጀመር፣ ገቢዎች ግብር ሲቆልል (😂) …ወዘተ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ጫና የሚፈጥሩት ነገሮች አብረው የሚቆዩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ትዳር ውስጥ ያለ ጭቅጭቅ፣ ነዝናዛ አለቃ…ወዘተ። ሰዎች Adjustment disorder እንዲያጋጥማቸው የሚያደርጉት መጥፎ ነገሮች ብቻ ሳይሆኑ ጥሩ ነገሮችም ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ትዳር መያዝ፣ ድንገት ሀብታም መሆን፣ ሹመት …ወዘተ።
ሰዎች ጫና ሲያጋጥመን የምንሰጠው ምላሽ እንደየመልካችን ይለያያል። ለአንዳንዶች በጣም የሚያስጨንቃቸው በሌሎች አይን በጣም ቀላል ነው። ይህንን የሚወስነው አስተዳደጋችን፣ የምንጠቀማቸው ራስን የመደለያ መንገዶች (Defence Mechanisms)፣ ያለን ማህበራዊ ድጋፍ …ወዘተ ነው።
የAdjustment disorder ህክምና በዋናነት የንግግር የስነ ልቦና ህክምና ሲሆን በጣም አልፎአልፎ ለጥቂት ቀናት ለእንቅልፍ የሚያግዙ መድሀኒቶች ሊሰጥ ይችላል።
ሰይፉ ፋንታሁን ስለ አእምሮ ህክምና በግልፅ ስለተናገርህ ከልብ አመሰግናለሁ። ካንተ ምስክርነት ማግለልና መድልኦን ፈርተው ሳይታከሙ በየቤቱ የሚሰቃዩ ወገኖቻችን የአእምሮ ህመም ማንም ላይ ሊከሰት የሚችልና ውጤታማ ህክምና ያለው ነገር እንደሆነ እንደሚረዱ ተስፋ አለኝ።
ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!!!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው