
ሕዝባዊ በዓላትና ሰንደቅ ዓላማ፤ የዓመቱ የአደባባይ ሕዝባዊ በዓላት በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች የሚያከብሯቸው የአደባባይ ክብረ በዓላት በመጡ ቁጥር ከበዓሉ ባልተናነሰ አጀንዳ ከሚሆኑ ጉዳዮች አንደኛው የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ነው።
ከሕዝብ ጋር በተለይም ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ዜጎች ጋር ብሽሽቅ መግባትን ልማዱ ያደረገው አገዛዙ በሕዝባዊ በዓላት ኮከብ የሌለበትን ሰንደቅ ዓላማ እንዳትይዙ የሚል ትዕዛዝ ማውጣትን ልማዱ አድርጎታል። ከሀርሞኒካ ጭፈራው፤ ከደመራው መውደቂያ አቅጣጫ እኩል የታለ ኮከቡ የባንዲራው ዓይነት የፀጥታ አካላት ከምዕመናን ጋር የሚፈጥሩት ንትርክ የበዓሉ አንደኛው ገጽታ እስኪመስል ድረስ የተለመደ ሆኗል።
ግን ግን ፖሊስ ምን አግብቶት ነው መሰል ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው? ምንድንስ ጥልቅ አድርጎት ነው የታል ኮከቡ አባሮሽ የሚገጥመው? የበዓሉ ፀጥታ አስከባሪ እንጂ የበዓሉ ባለቤት አይደለ?! የክብረ በዓሉ ባለቤቶች ምዕመናን ናቸው። ምዕመናን በራሳቸው ድግስ ደስ ያላቸውን ቢይዙ ማን ሊከለክላቸው ነው? ኮከብ ያለው የሌለው ሥርዓት ማስከበርን በመንግስታዊ ተቋማት ከማስከበር በስተቀር በቤቴ፣…በጥምቀቴ…ብችል የዓለም አገራትን ሰንደቅ ዓላማ ባውለበልብ… ይዤ ለአምልኮ አደባባይ ብወጣ ማን ሊከለክለኝ ኖሯል? አንዳንድ ክልከላዎች ከትሕነግ ጋር መቃብር መውረድ ያለባቸው መሆናቸውን ማስታዎስ ግን እፈልጋለሁ።
የግርጌ ማስታዎሻ፦ የጥምቀቱ ባለቤቶች ሆይ ከቻላችሁ የመላው አፍሪካውያን ሰንደቆችን እና የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራትንም ሰንደቆች ጨምራችሁ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት ክብረ በዓል ዓለምአቀፋዊ ገጽታ እንድታላብሱት ማስታወስ እፈልጋለሁ። ወዲያውም አፍሪካውያንና ሌሎች ወዳጆቻችን ከኢትዮጵያችን ጎን በመቆም ላሳዩት ወንድማማችነት ክብር መስጠት ይሆናል። በበኮከብም ያለኮክብም አገርና ሕዝብን ለምታስቀድሙ ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋና ለእናንተ! መልካም ከተራ! መልካም ጥምቀት!