
የ1953ቱን መፈንቅለ መንግሥት ከመሩትና ካስተባበሩት ሰዎች መካከል ከዋነኞቹ ተርታ ተሰላፊ ነው ብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ። የገርማሜ ንዋይ ታላቅ ወንድም ጀነራል መንግሥቱ የተወለደው በ1909 ዓ.ም ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ነበር። በኋላም ሆለታ ለተቋቋመው ገነት ጦር ትምህርት ቤት ወጣቶች ሲመለመሉ ከተመለመሉት ወጣቶች መካከል አንዱ ሆኖ ጦር ትምህርት ቤቱን የተቀላቀለው መንግሥቱ፣ ከአንድ ዓመት ስልጠና በኋላ በ1928 ዓ.ም በምክትል መቶ አለቃ ማዕረግ ተመረቀ። ይህ ጊዜ ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን የወረረችበት ጊዜ ስለነበር የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ወጣት መኮንኖች ወደ ማይጨው ሲዘምቱ መንግስቱም አብሮ ዘመቷል።
በማይጨው ጦርነት የኢትዮጵያ ጦር ሲፈታ ወደ ነቀምት ሸሽተው የጥቁር አንበሳን ማኅበር ከመሰረቱት አባላት መካከል መንግሥቱ ንዋይ አንዱ ነበር። ቀጥሎም ወደ ጅቡቲና ሱዳን ከተሰደደው ሰራዊት ጋር አብሮ በመሰደድና በካርቱም የወታደራዊ ተሀድሶ ሥልጠና በመውሰድ በ1933ዓ.ም. አጼ ኃይለሥላሴ በእንግሊዞች ድጋፍ ሰጪነት በኦሜድላ በኩል እየተዋጉ ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ መንግሥቱ ንዋይም አብሮ እየተዋጋ ለሀገሩ ምድር በቃ። አልጋ ከተመለሰ በኋላ በጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ ስር በሻምበልነት የክቡር ዘበኛ አባል ሆኖ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሆነው ሲመደቡ መንግሥቱ ብርጋዴር ጄኔራል ተብለው የክብር ዘበኛ ጠቅላይ አዛዥነትን ተሾሙ።
“የትላንት ወንጀለኛ የዛሬ ባለታሪክ” – የነ መንግሥቱ ንዋይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ታሪክ ነው። ትልቅ ታሪክ! በተደጋጋሚም ተጽፏል ፣ተተርኳል፣ተተንትኗል። እንደዚህ ዓይነት የታሪክ አንጓዎች ጥለውልን የሚሄዱት ብዙ ነገር አላቸው። መመርመሩ የኛ ፈንታ ነው ። ከ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ዋነኛ የዋናዮች አንዱ የሆነው ብ/ጀ መንግሥቱ ንዋይ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ትቶልን ከሄደው ነገር አንዱ በፍርድ አደባባይ ያደረገው የመጨረሻ ዲስኩሩ ነው። የትላንት ወንጀለኛ የዛሬ ባለታሪኩ መንግሥቱ በሚፈርዱበት አላዘነም ፣አዘነላቸው እንጂ! ይግባኝ አልጠየቀም፣ወደ ሞት በክብር ሄደ እንጂ! ልክ እንደ ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጥስ…..ሶቅራጥስ በፍርደ ገምድል ሞት ሲፈረድበት ‹‹I am going to die; you are going to live. Which one is better? Only God knows›› ነበር ያለው። መንግሥቱስ? ‹‹እኔ ግን በደስታ ወደ ሞት እሄዳለሁ››
የመንግሥቱ የመጨረሻ ዲስኩር ሊመረመር የሚገባው ታሪክ ነው። እነሆ ትንቢተ-መንግሥቱ ንዋይ….‹‹እናንተ ዳኞች! የበየናችሁብኝን የሞት ፍርድ ያለ ይግባኝ ተቀብያለሁ። ይግባኝ ብዬ የሚመለከትልኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢሆን ኖሮ ይግባኝ ማለት በፈልግሁ ነበር። ነገር ግን ይህ እንደማይሆን አውቃለሁና የአፄ ኃይለ ሥላሴን ፊት ለማየት አልፈቅድም። በእግዚአብሔር ስም በተቀመጣችሁበት የፍርድ ወንበር ላይ ከመቀመጣችሁ በፊት በእኔ ላይ የምትሰጡትን ፍርድ ታውቁት እንደነበር ሳስበውና ፍርድ እስከዚህ መድረሱን ስታዘብ ሀዘኔ ይብሳል።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ ነጻነትና እርምጃ የተነሳሁ ‹ወንጀለኛ› ነኝ እንጂ ላፋጀው የተነሳሁ ወንበዴ አይደለሁም። ይህን ማድረግ ፈልጌ ቢሆን ኖሮ ማንም የማይወዳደረው ሠራዊትና መሣሪያ ሳላጣ ዛሬ ከእናንተ ፊት ለመቆም ባልበቃሁ ነበር። እኔ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ድንክ ውሾች ያነሰ ደመወዝ የሚያገኙ ሁለት ተራ ወታደሮችን አጣልቼ ለማደባደብና ሀገር ለማፍረስ አለመነሳሳቴን የሚያረጋግጥልኝ ከእናንተ በትዕዛዝ ያገኘሁትን ፍርድ ለመቀበል እዚህ መቆሜ ነው።
ከእኔ በፊት በግፍ የፈሰሰው የንፁህ የኢትዮጵያዊያን ደም ብዙ ነው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ግፍ ሽልማት በመሆኑ እኔ ለመሞት የመጀመሪያው ሰው አልሆንም፡፡ ሥልጣን አላፊ ነው፡፡ እናንተ ዛሬ ከጨበጣችሁት የበለጠ ሥልጣን ነበረኝ፤ ሀብትም አላጣሁም፡፡ ነገር ግን ሕዝብ የሚበደልበት፣ ሥልጣንና ድሃ የማይካፈለው ሀብት ስላልፈለግሁ ሁሉንም ንቄ ተነሳሁ። አሁንም እሞታለሁ፡፡ ሰው ሞትን ይሸሻል፤ እኔ ግን በደስታ ወደሞት እሄዳለሁ፡፡ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅነት ቀድመውኝ መስዋዕት የሆኑትን አብረውኝ ተነስተው የነበሩትን ጀግኖች ወንድሞቼን ለመገናኝት ናፍቄአለሁ፡፡
የጀመርኩት ሥራ ቀላል አይደለም። ነገር ግን አልተሸነፍኩም። ወገኔ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀመርኩትን ሥራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፈጽሞ እራሱን እንደሚጠቅምበት አልጠራጠርም። ከሁሉ በበለጠ የሚያስደስተኝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልሠራለት ካሰብኳቸው ሥራዎች አንዱ የኢትዮጵያን ወታደር ዋጋና ክብር ከፍ ማድረግ ሲሆን ይህ ሀሳቤ ሕይወቴ ከማለፉ በፊት ሲፈፀም ማየቴ ነው፡፡
ዛሬ መኖራችሁን በማየቴ ነገ መሞታችሁን ረስታችሁ ‹አሜን› ብላችሁ ቀናችሁን በማስተላለፍ በመገደዳችሁ በእኔ ላይ ሳትፈርዱ በራሳችሁ ላይ የፈረዳችሁ መሆናችሁን አላስተዋላችሁም፡፡ እኔ የተነሳሁት ከትክክለኛ ህግና ከህሊናችሁ ውጭ ለመፍረድ እንዳትገደዱ ለማድረግ ነበር፡፡ ባጭሩ በእኔ ላይ ለመፍረድ የቸኮላችሁትን ያህል አሥር እና አሥራ አምስት ዓመት የምታጉላሉት የድሀውን ሕዝብ ጉዳይ እንደዚህ አፋጥናችሁ ብትሠሩትና ብትሸኙት ኖሮ የእኔ መነሳት ባላስፈለገ ነበር። ከእናንተ ከዳኞችና የሞት ፍርድ እንድትበይኑብኝ ካዘዛችሁ ሰው ይልቅ ፍርድ ተቀባይ የዛሬው ወንጀለኛ የነገው ባለታሪክ ነኝ። የኔ ከጓደኞቼ መካከል ለጊዜው በሕይወት መቆየትና ለእናንተ ፍርድ መብቃት የመመዘኑን ፍርድ ለመጭው ትውልድ የሚያሳይ ይሆናል፡፡
ዋ ! ዋ ! ዋ ! ለእናንተና ለገዢያችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃሳቤ በዝርዝር ገብቶት በአንድነት በሚነሳበት ጊዜ የሚወርድባችሁ መዓት አሰቃቂ ይሆናል፡፡ በተለይ የአፄ ኃ/ስላሴ የግፍ መንግስት ባላደራዎች ሆነው ድሀውን የኢትዮጵያ ህዝብ ሲገሸልጡት ከነበሩት መኮንን ሀ/ወልድና ገ/ወልድ እንግዳወርቅን ከመሳሰሉት በመንፈስ የታሰሩ በስጋ የኮሰሱ መዠገሮች መካከል ጥቂቶቹን ገለል ማድረጌን ሳስታውስና የተረፉትም ፍፃሜያቸውን በሚበድሉት በኢትዮጵያ ህዝብ እጅ ላይ መውደቅ ሲሰማኝ ደስ ይለኛል፡፡››