
በሀገራችን የዲሞክራሲ ትግል ውስጥ ትልቁ ፈተና ኢ-ዴሞክራሲያዊና አምባገነን መንግስታት ብቻ አይደሉም። የሴራ ምሁራንም ጭምር እንጂ። በገዛ ራሳችን ምሳሌ “ቀና ቀና ያለች ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ” እንደ ተባለው የሀገራችን የሴራ ምሁራን ከመካከላቸው ቀና ያለውን በማጥቃት ብዙ ፍሬ ያዘሉ ሰብሎቻችንን አምክነው ኖረዋል። በዚህ ድርጊታቸው ከአምባገነን መንግስታት በላይ ሀገራችንን መከራ ውስጥ ጨምረዋል። — ብርሀኑ ነጋ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የመፍትሄ ምንጭ እንጂ ጸረ ኢትዮጵያዊ ወይም ጸረ ኢትዮጵያ ተብሎ ለተከታታይ አመታት በአደባባይ የሚዘመትበት ሰው አልነበረም።
ብርሀኑ ከጽንፈኛ ብሄርተኞችና ከአክራሪ ሀይማኖተኞች በሚወረወርበት ሾተል ጀርባው እየደማ የዜግነት ፖለቲካን የሙጥኝ ያለው ‘በኔ ጉዳት ኢትዮጵያ ትዳን’ ብሎ እንጂ ኢትዮጵያን ስለሚጠላ አይደለም!
እንዲህም ተባለ እንዲያ ዛሬ ያ መገፋቱ ፍሬ አፍርቶ እነሆ ከሶስት የጭለማ አመታት በኋላ ሀገር ኖራ፣ ምርጫም ኖሮ፣ ወደ ፊት ልንሻገር ነው ብለን የምናስብበት የተስፋ ጭላንጭል ላይ ደርሰናል።
ምርጫ አለ ያልነው ብርሀኑ ስላለ ነው! ኢትዮጵያ ያንን ሁሉ መከራ አልፋ ለምርጫ የደረሰችው ብርሀኑ ነጋ በፖለቲካ ስም ሀገር የመናድ የገመድ ጉተታው አካል ስላልነበረ ነው!
ዶላርና የጥይት አረር ታቅፈው ከውጭ የገቡ ተቃዋሚዎችና ሚሳኤል የታጠቀች ህወሀት “ህገ መንግስቱን ትነኩትና” እያሉ በሚያስፈራሩበት በዚያ የሶስት አመት ጭለማ ክረምት ውስጥ ህዝብ ብርሀኑን ሰምቶ “እውነት ነው ጊዜው የህገ መንግስት ጥያቄ ማንሻ አይደለም” ብሎ ጋብ ባይል ኖሮ፤ “ይህ የምንፈልገው ስርዓት አይደለም፣ ይሁን እንጂ ለሀገራችን ስንል እንደግፈው፣ ከችግሮቹ ይልቅ ጠንካራ ጎኖቹን እያሳየን ወደ ፊት እንግፋው” ብሎ ከመንግስት ጎን ቆሞ “አለሁ!” ባይል ኖሮ የዛሬው የምርጫ ክርክር ቅንጦት በሆነ ነበር።
በእውቀቱ ልክ እያሰበ በሀገር ፍላጎት ልክ እየወሰነ ባይራመድ ኖሮ “በለው በለው – ፍለጠው ቁረጠው” ባዮች ጋር በስሜት ጋልቦ ቢሆን ኖሮ…… እንኳን አንግቦት የተነሳውን የዜግነት ፖለቲካ ለአካለ ምርጫ ማድረስ ይቅርና ለሀገራችንም ጦስ በሆነ ነበር።
ይህ ሁሉ ለህዝብ ግልጽ የሆነ ሀገራዊ አበርክቶው በሴራ ምሁራን ትንታኔ እየታጀለ ቀን ከሌት መዶስኮሩ ሰውዬው በእርግጥም ፍሬ ያዘለ ሰብል መሆኑን ከማሳየቱ በቀር እንደሚሉት ጥላቻ በልቦናው የተሸከመ ጸረ ህዝብና ጸረ ሀገር መሆኑን ፈጽሞ አይመሰክርም!
ይድረስ ለብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) የመጨረሻ ውጤቱ፣ ጥራቱና መጠኑ ምንም ይሁን ምን፣ ዴሞክራሲን አዋልደሀል!! ጨቅላውን ዴሞክራሲ አንስቶ መሳም፣ አቅፎ ማሳደግ የኛ ድርሻ ይሆናል! ለዘመናት የተጫነብንን የዘር ፖለቲካ የምናራግፍበትን አንድ ዘዴ የሆነውን የዜጋ ተኮር ፖለቲካ አስተምረህ፣ አዋቅረህ፣ ከምርጫው ኮሮጆ አድርሰህልናል – ያለፈውን ጥፋት ላለመድገምና እንደ ቀሪው አለም በሀሳብ ላይ መሰረት ያደረገ ፖለቲካን መምረጥ የኛ ፋንታ ይሆናል። በብዙ መከራዎች መካከል ባለች ሀገር ውስጥ የሰከነ የተቃውሞ ፖለቲካን በማራመድ ሀገርና መንግስት በፈለጉን ጊዜ አቤት እያልን በቀረው ደግሞ እየተቃወምንና እየተቸን መጓዝ የምንችልበትን የሰለጠን አስተሳሰብ አሳይተኸናል። ይህን መንገድ ተከትሎ ያለጩኸት እና ያለ ወከባ መንግስት መቀያየርን መልመድ የኛ ተግባር ይሆናል።
በቀረው ደግሞ ምርጫው በሰላም ተጠናቆ ቢሆን በፓርላማው፣ ከዚያም ሲያልፍ በመንግስት ስልጣን ላይ ሆነህ ቀሪ ህይወትህን ለዚህች ደሀ ሀገራችን የበለጠ እንድትሰራ መልካም ውጤት እመኝልሀለሁ! በቀረው ግን ውለታህ አለብን እንጂ ግዴታችን የሌለብህ ከሚጠበቅብህ በላይ ያገለገልከን ታላቅ ዜጋ ነህና እናከብርሀለን