
አምና ይሄን ጊዜ “ታሪካዊ መብቴ ከአባይ ውሀ ላይ በማንኪያ ተነክቶ፣ ተኝቼ አላድርም ምን ሲደረግ ከቶ!” እያለች ግብጽ ስትዝትብን ጦሯን እያሳየች ስታስፈራራን “ይሄ ሰው ያሳልፈን ይሆን?” እያልን እኛ ስንጨነቅ፣
አቶ ስዩም መስፍን “ግድቡ ተሽጧል” እያለ ሲሳለቅ በፍርሀትም በጥርጣሬም ሆነን “ምን ያደርገን ይሆን?” ስንል አባይ ተገደበ፣ ውሀው ተከተረ።……. አለፍነው!!
ተመስገን!!….. ብለን ሳለን ገና መዘዘኛው ኮረና ተንኳቶ ሲገባ ምርጫው ይዘግይ ሲባል ደግሞ ፦“ከመስከረም ሰላሳ በኋላ ያባ ቢላዋ ልጅ ሀገር አታስቡ፣ ኢትዮጵያ ፈርሳለች ቁርጣችሁን ስሙ” እያሉ የሀገር መፍረስ መርዶ ገና ከሩቅ ሲያረዱን …
“አይ ደግሞ ጣጣችን “ምን ያደርገን ይሆን?” እያልን ስንፈራ፣
ሀገር ከርማ አደረች አበራን ደመራ…።
መቼም ጣጣችን ብዛቱ፣ የሁለት አመቱ። ደግሞ እንደ ገና ወያኔ ጎፈላች፣ ዘንድሮ ጨርሱኝ አልሰነብት አለች…ፈራን፣ በጣም ፈራን፣ የሀገር ምሶሶ ወደቀብን እያልን በጭንቀት ሰማይ ምድሩን ቧጠጥን፣ ጾም ጸሎት ምህላ ገባን…ተሰማን! የልመናችን ውጤት ደረሰ። — ወያኔ በጫረችው እሳት ተለብልባ ጠፋች።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እነዚህ ሁሉ ጊዜ በማይረሳው ቀለሙ የከተባቸው አሻራዎችዎ ናቸው።
— (የመጨረሻ መጨረሻ) …..
ይህ ከፊታችን የሚጠብቀን ብሄራዊ ምርጫ ያለ አንዳች መንገራገጭ ያለምንም ጉርምርምታ በሰላም ቢጠናቀቅ……. እንዳሉንም አብይ አህመድ ኢትዮጵያን አሻገራት ብለን እንመሰክራለን! የምትታየው ጭላንጭል ዴሞክራሲ አንድ እርምጃ እንዲራመድ ስለማድረጎ በታሪክ ፊት እንናገራለን። አረረም መረረም ከኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ የሚገኘውን ውጤት ተቀብለው አዲስ ዴሞክራሲያዊ መንግስት እንዲመሰረት እድል አመቻችተዋልና “እኔ አሻግራችኋለሁ” እንዳሉን ቃሎን ጠብቀዋልና……. በዚህ የታሪክ ተጠቃሽ ይሆናሉ!! ኢትዮጵያ ይህን በተስፋ ትጠብቃለች!!