
የስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የቅድመ ምርጫ ሂደት በብዙ ችግሮች እና ውጣውረዶች የተሞላ እና መሰረታዊ የምርጫ ሂደቶችን የማያሟላ ነው ሲሉ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ተናገሩ። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፣ ሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና እናት ፓርቲ በጋራ ባወጡት መግለጫ የቅድመ ምርጫ ዳሰሳ ሂደቱ በመራጮች ምዝገባ፣ በታዛቢዎች አያያዝ፣ በምርጫ ቅስቀሳ ከፍተኛ ችግር ከማስተናገዱ ባለፈ የዕጩዎች ግድያ፣ የፓርቲ አባላትና ደጋፊዎች መዋከብ፣ እስር እና እንግልት በጉልህ የተስተዋለ ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳው ያስፈልጋል በማለት የጋራ ነው ያሉትን አቋማቸውን ይፋ አድርገዋል።
ምርጫው በሁለት የተለያየ ጊዜ መከናወኑም በሂደት መንግሥት ለመመስረት የሚደረገውን ሥራ የሚያወሳስብ ነው ብለዋል።መግለጫው በቀጣይ የሚከናወኑ የተለያዩ ሥራዎች በተሻለ አፈፃፀም እንዲከናወኑ ለማድረግ ያግዛል ያሉት አምስቱም ፓርቲዎች ሂደቱ ዝቅተኛውን መስፈርት አያሟላም ካላችሁ መሳተፋችሁ ለምን ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሂደቱ መሳተፍ በራሱ አገርን የሚጠቅም ነው በማለት ከምርጫው ራሳቸውን የማግለል ውጥን እንደሌላቸው ተናግረዋል።