
ምንም እንኳ ከልጅነቴ በወጣ ገባ ባውቃትም ኑሮዬ ብዬ የከተምኩባት ግን ከምርጫ 97 ሳምንት በኋላ ነው። ከዝያ በኋላ ደግሞ ወያኔ ቂም ቋጥራ በቀል ሰንቃ የዘመተችባት ጊዜ ነበር – አዲስ አበባ።
አዲስ አበባ ስሟና ግብሯ እንዳይገናኝ ተደርጋ ወደ ሸታታ የአምቡላ በርሜልነት ሙሉ በሙሉ የተቀየረችው ከምርጫ 97 በኋላ ነበር። አይኔ እያየ ሜዳዎች እየታረሱ እንደ ክብሪት እቃ በሚደረደሩ የኮብልስቶን ህንጻዎች መሞላት ጀመሩ።…. ነዋሪው እግሩ ከመኖሪያ ቤቱ ሲወጣ የሚያርፈው አውራ ጎዳና ላይ ብቻ ሆነ። የአይን ማረፍያ፣ የአዕምሮ ማሳረፍያ፣ የመቆዘሚያ መስኮች በቅጽበት እንደ ቤንዚን እየተነኑ ይጠፉ ጀመር። …… አካባቢዎች ወደ ተለያዩ ግማቶችና አስቀያሚ ሽታዎች ተቀየሩ።……
ከስራና ከትምህርት መልስ ወዴት እሄዳለሁ? የእግር ጉዞ ለማድረግ መንገዶች ተጨናንቀዋል። የእግረኛ ማሳለጫ መፈናፈኛ የለም። ያለው አማራጭ ድራፍት ቤት መሰየም ነው። ቅዳሜና ዕሁድ ቢያንስ ሁለት ጊዜ አራዳ ህንጻ እመላለሳለሁ። ጠዋት በማኪያቶ ከሰዓት በጃምቦ ድራፍት — ከዚያ ውጪ የት መሄድ እችላለሁ?……..
አንድ ጊዜ ጎልፍ ክለብ ሄጄ አይቼ ከደስታዬ ብዛት አይኖቼ በእምባ መሞላታቸውን አስታውሳለሁ። ሰፊ ሜዳ፣ የመሮጫ የመጫወቻ መስክ ብርቅ ሆኖብኝ ነበር። እንደዚያ አይነት ነገር ሳላይ በጣም ቆየሁ። የመስተንግዶ ስፍራውን ትቼ ሳሩ ላይ በደረቴ ተኛሁ። ይህን በወር ስንት ጊዜ ላየው እችላለሁ? አቅም የለኝም። ያንን ቀንም ተጋብዤ ነው እዚያ ከፍ ያለ የባለጸግነት መለኪያ የተባለ ስፍራ የሄድኩት።….
ሌላ ጊዜ ወደ ሲ ኤም ሲ የሚገኝ አንድ የፈረስ መጋለቢያ መስክ ሄጄ አይቼ ተደመምኩ። …. ላለው ስፍራ አለው። ለኔስ? ድሀና ሀብታም መሆኔ ሳይለካ እንደ ዜጋ የማገኘው ሜዳ፣ ንጹህ መስክ፣ ነፋሻ አየር፣ ከጫጫታው የምርቅበት፣ አይኖቼ የሚመለከቱት ተፈጥሯዊ ስፍራ.. ለኔስ?….
ከዝያ በኋላ ካምፓላ፣ ናይሮቢ፣ ዳሬሰላምን አየሁ፣ በቅናት አበድኩ። ……ኢትዮጵያ – እንዴት እንደ ተሰበርን፣ እንዴት እንደ ተናቅን፣ እንዴት የቆሻሻ መጣያ እንዳደረጉን አስቤ በሀገሬ ሁኔታ ተስፋ ቆረጥኩ። ይልቁንም የኬኒያ ዋና ከተማ በናይሮቢ መሀል የሚገኘውን በብዙ ሺህ ሄክታር ላይ ያረፈ የህዝብ መዝናኛ ስፍራ በየትኛውም ዘመን የሚነሳ መንግስት ይህንን ስፍራ እንዳይሸጥ እንዳይለውጥ የህዝብ ሆኖ እንዲቀጥል በህገ መንግስት እስከ መደንገግ የተደረሰ መሆኑን ስሰማ…… እነ ኡጋንዳ የህዝብ ብለው የያዟቸው ገና ያልለሙ በርካታ ስፍራዎች በየከተሞቻቸው መሀል አጥረው እንዳስቀመጡ ሳውቅ……. አዲስ አበባን አስቤ ቅስሜ ተሰብሯል።
በአንድ ወቅት አብራኝ የምታስተምር የውጭ ሀገር ዜጋ ስለ ከተሞች ስናወራ “Addis Ababa, a city in a dirt” የሚል የቢቢሲን ዘገባ ስታስነብበኝ ተከራከርኳት። “ስለሚጠሉን ነው” ብዬ አዲስ አበባ ከነችግሯም ቢሆን ውብ ነች እያልኩ የተከራከርኩበትን ጊዜ አስቤ መሳሳቴ ይበልጥ ገባኝ።›….
ዛሬ አዲስ አበባ የምፈልገውን ያህል በሌሎች ከተሞች ያየሁትን ያህል አይደለም፣ ግን እየታጠበች ነው፣ እየጸዳች ነው። ይህን መካድ አይቻልም። ዛሬ የኔ ነው የኔ ነው እያልን የምንከራከርበት መስቀል አደባባይ የስፖርትና የኮንሰርት ስፍራ ብቻ ሳይሆን የአደንዛዥ እጽ መሳቢያ፣ የሲጋራ ማጨሻ፣ የወንጀል ሰንሰለት ማበጃ እንደነበረ ሁላችንም እናውቃለን። ይህ ስፍራ መጽዳቱ ከውበቱ ባሻገር ናሙናው ሌሎች አደባባዮችን በመአዛው አውዶ ለጽዳት እንደሚያነሳሳቸው እናውቃለን።
የእንጦጦ ገጸ በረከት ለአዲስ አበባ ነዋሪ ምን እንደሆነ ለመረዳት እነዚያን መሄጃ አሳጥተውን ዛፍና ደን የገጠር ስጦታ ብቻ እየመሰላቸው በህንጻ ላይ መንጠላጠልን የከተሜነት የስልጣኔ ምልክት አድርገው ከተፈጥሮ ያራራቁት እስኪመሰክሩልን አንጠብቅም፣ ሌሎችም በዚህ ሁለት አመታት ያየናቸው ተፈጥሮንና ውበትን ማዕከል ያደረጉ ፕሮጄክቶች አዲስ አበባን የሚመጥኑ ከተማዋን የሚገባት እና ለአመታት ተነፍጋቸው የነበሩ ናቸው።…….
ምንም እንኳ ከተማይቱ ቆሻሻ በልተው ቆሻሻ ውስጥ የሚኖሩ በርካታ ዜጎችን አቅፋ የኖረች ቢሆንም፣ የነዋሪው ጥያቄ ተቆጥሮ የማያልቅና ውስብስብ ቢሆንም፣………በዚህ ፍጥነት ነዋሪውን ማዕከል ያደረገ ተፈጥሮን የመመለስ እና የከተማዋን ውበት የማድመቅ ተግባር ትናንት “በግማት ውስጥ ያለች ከተማ ያሏትን አለማቀፍ ሚዲያዎች “The City in a Park” ብለው እስኪደመሙባት ድረስ ሊቀጥልና ነዋሪውም ይህን ሀብቱን በእንክብካቤ ሊጠብቅ በሰለጠነ መልኩ ሊጠቀምባቸው፣ እናም ሊመስላቸው ይገባል ባይ ነኝ!
የትነበርክ ታደለ – መምህርና ጋዜጠኛ